መግቢያ |
እንኳን ደህና መጡ! - Welcome!
"ታላቅ እንደነበርን፣ ታላቅ እንሆናለን!" አገራችን ኢትዮጵያ ምንም እንኳ ቀደምት የስልጣኔ አገር ብትሆንም በዚህ ዘመን በበርካታ ነገሮች ከሌሎች አገሮች ጋር ለንንፅር ስትቀርብ ኋላ ቀር መሆኗ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ይህ ማለት ግን ተስፋ የሌላት ደካማ አገር ነች ማለት አይደለም፡፡ ያላትን ጥሬ ሀብት በትክክል ከተጠቀመችበት አይደለም ለራሷ ለሌላው አለም የምትተርፍ ድንቅና ግሩም አገር እንደምትሆን የራሷ ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ የውጭ ዜጎች ጭምር ያምናሉ፡፡ ጥንታዊ ድርሳናትን በውብና ማራኪ ፊደላት ከትባ በውስጧ ታቅፋ የያዘቸው ይህች አገር እንደቀድሞ ገናናነቷ በነበራትና ባላት ነገር ላይ አመርቂ ዕድገት እያሳየች ባለመሄዷ ስልጣኔዋ የተገታ ሊሆን ችሏል፡፡ በዚህ የዲጅታል ቴክኖሎጂ ዘመን ላይ ደርሰን እንኳ ለሌላው አለም ትምህርት መስጠት የምንችልበትን ሁኔታ መፍጠር ስንችል ጉዟችን ዘገምተኛ ሆኗል፡፡ የመረጃ አያያዛችንንና አጠቃቀማችንን ስንፈትሸው ከአገራችን ታሪካዊ አመጣጥ ጋር ተመጣጣኝ ሆኖ አናገኘውም፡፡ እንኳን ልናሳድገው ቀርቶ ያለንን ተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ሀብት በአግባቡ ተንከባክበን አልያዝነውም፡፡ ይባስ ብሎ እኛው በእኛው አጥፊ ሆነን የምንታይበት ሁኔታ ይታያል፡፡ አለም ገና ሳይሰለጥን የኢትዮጵያ ቀደምት አባቶችና እናቶች ስለአገራችን ህልውና አስበውና ተጠበው ለእኛ ለተተኪ ትውልዶቻቸው በድንጋይና በብራና ላይ ፅፈው ያስተላለፏቸው መልዕክቶች እነሱ በጀመሩት ሀሳብ ላይ እኛም እንድንቀጥልበትና ተጨማሪ ዕውቀት ለሌላውም እንድናስታላልፍበት አስበው ነበር፡፡ ይህንን ጥበባዊ ሀብት ሌላው አለም አልታደለም፡፡ እኛ ግን ከስንፍና የተነሳ ምን አድርገን ወደተሻለ ደረጃ ላይ ማድረስ እንዳለብን ሳናውቅበት እየኖርን እንገኛለን፡፡ ጭራሽ በባህር ማዶ የሚኖሩ የሌላ አገር ሰዎች የእኛን ቅርስ ለማስጠበቅ ሲታገሉ የምናስተውልበት ጊዜ አለ፡፡ ኢትዮጵያ ትልቅ አገር ነች፡፡ ልጆቿ አፍ አውጥተው ስለአገራቸው ማንነትና ምንነት ሳይናገሩ ድንጋይና አፈሩ ሁሉ ሳይቀር ብዙ ነገር ይናገራል፡፡ ተፈጥሮ ሳይቀር እጅጉን ለኢትዮጵያ ያደላል፡፡ በዚህ ፀጋ መሀል ተቀምጠን የሚወጣና የሚገባውን፤ የሚሄድና የሚመጣውን ነገር ዘግበን የማስቀመጥ ልምዳችን አናሳ ነው፡፡ ትውልድ ግን ነገም እንደ አዲስ ይመጣል፡፡ መጭው ዜጋ የሚረከበው ነገር ከሌለ አዲስ ነገር ለመፍጠር ይከብደዋል፡፡ ቅብብሎሽ ያስፈልጋል፡፡ አንድን ነገር ለመወራረስ ትልቁ መገናኛ ዘዴ ደግሞ መረጃን በአግባቡ ይዞ ለሌላው ማስተላለፍ ሲቻል ነው፡፡ ክፍተትን ማጥበብ የሚቻለው ቀድሞ የተሰሩ ነገሮች ምን እንደሆኑ ተጨባጭ በሆነ ማስረጃ በማቅረብና መሞላት የሚገባው ጉድለት ካለ የመፍትሄ ሀሳብ በማምጣት የተሻለ የአኗኗር ስርዓት በመፍጠር ነው፡፡ ዕውቀት የሚመነጨው ትክክለኛ መረጃ አሰባስቦ በመያዝና ስለጉዳዩ ክትትል በማድረግ ነው፡፡ የነበረን ነገር አስጠብቆ መያዝ አንድ ነገር ሲሆን ባለ ነገር ላይ አዲስ ሀሳብ መጨመር ደግሞ ውጤታማ የዕውቀት ሽግግር ይሆናል፡፡ ታዲያ ይህንን ክፍተት ለመሙላት የተራራቀውንና የተዘበራረቀውን አሰራር በመጠኑም ቢሆን በማስተካከል ለሀገራችን ከሁላችን የሚጠበቅ ድርሻ አለብን፡፡ እርግጥ ነው በሀገራችን አንድን ነገር ለመስራት አድካሚ ጉዞ ይጠይቃል፡፡ ብዙ የጎደለ ነገር ስላለ ሳይሆን የተቀናጀ አሰራር ባለመኖሩና የትብብር መንፈስ ስለሌለን እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡ እናም ያለንን ነገር በመፈተሽ መሟላት የሚገባውን ጉዳይ ለማስተካከል አነሳሳችን በመረጃ ላይ የተደገፈ ቢሆን ይመረጣል፡፡ ከዚህ በተረፈ በመረጃና በዕውቀት መመላለስ ጠቃሚ መሆኑ እንዳለ ሆኖ በይበልጥ መልካምነትንና በጎነትን እያሰቡ መስራት የዚህ ዘመን ዋነኛ ተፈላጊ ነገር እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ መንፈሳዊ እሴቶች ለዘመናችን ትውልድ ከምንም በላይ አስፈላጊ ናቸው፡፡ የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ ማንነቱን አስጠብቆ ሳይንሳዊ የቴክኖሎጂ ውጤቶችንም በአግባቡ ሊጠቀም ይገባል፡፡ አለማችን ላለፉት መቶ አመታት በፈጣን የስልጣኔ ዕድገት ውስጥ የመጣች ሲሆን ከዚህ በኋላም በሚኖራት ጊዜ ከቀደመው በበለጠ በአዳዲስ ግኝቶች እንደምትሞላ እርግጥ ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ሁሉ እንቅስቃሴ አገራችን ኢትዮጵያም በልጆቿ የራሷን ሚና ልትጫወት ትችላለች፡፡ ይህም የሚወደድና የሚበረታታ ነገር ነውና መልካም ባህሎቻችንን በማስጠበቅ ከወዲሁ ከሌሎች አገራት ጋር መሳ ለመሳ መጓዝ ያስፈልጋል፡፡ |
Dear this website visitors, all the web pages are established in Amharic (Ethiopian) language font so please use or install Power Geez program in your PC in order to browse it properly if strange symbols appeared on your laptop when you open it. Otherwise please use translation tools. |
"ሰናይ ዓለም " የሬድዮ ፕሮግራም
የማስታወቂያ ስራ
የግንኙነት ስራ
የቢዝነስ መድረክ
የዲጅታል ስራ
የመፅሀፍ ግምገማ
"ሲላ" አጭር የመረጃ መፅሄት
"አላማ" ሽልማት
"ሀበሻ" ቤተ-መዘክር
|
|
|
|